History

ደብረታቦር!

የታቦር ተራራን መነሻ በማድረግ ስያሜዋን ያገኘችው ደብረታቦር በኢትዮጵያ ጥንታዊና ታሪካዊ ከሚባሉ ከተሞች መካከል አንዷ ናት።

ደብረታቦር የጥንት የበጌምድር መናገሻ ከተማ የነበረች በኋላም በዘመነ መሳፍንትና ከዘመነ መሳፍንት በኋላ በነገሱት የአጼ ቴዎድሮስ እና አጼ ዮሀንስ ዘመነ መንግስት ወቅት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በመሆን ያገለገለች ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ ናት።

ከተማዋ በ1327 ዓ/ም በአጼ ሰይፈ አርዕድ አማካኝነት እንደተቆረቆረች ይነገርላታል። ከዚህ ዘመን በኋላ ከተማዋ በርካታ ሂደቶችን አልፋለች። በቀደመ ስሟ ጁራ/ሰማራ እየተባለች ትጠራ እንደነበርና ነዋሪዎችም እጅግ ታታሪ ሰራተኞችና ጥበበኞች እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ደብረታቦር የበጌምድር ጠቅላይ ግዛት ገዥ በነበሩት በራስ ጉግሣ ወሌ ዘመን የከተሜነት ቅርጿ የዘመነና ኢትዮጵያ ውስጥ ሞቅ ያለ የገቢያ ስርአትና የህዝብ እንቅስቃሴ ከሚታይባቸው ከተሞች መካከል አንዷ እንደሆነች የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።

ደብረታቦር የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ጥማት ማስታገሻ፣ የአጼ ቴዎድሮስ የህልም መወጠኛ የመጀመሪያው የጋፋት የኢንዱስትሪ መንደር መገኛ ከተማ ናት። ደብረታቦር በርካታ ምንጮች ይገኙ እንደነበርና በተለይም ከ1890ዎቹ ጀምሮ የባህርዛፍ ተክል ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ብዙዎቹ ምንጮች እንደተዳከሙ ይታወቃል። ከደብረታቦር በቅርብ እርቀት የአፍሪካ የውሃ ማማ የሆነው የጉና ተራራ ይገኝበታል። የጉና ተራራ ከአራት መቶ በላይ ምንጮችና ከ40 በላይ ወንዞችን ይወጡበታል። ከጉና ወጥተው ለአባይ የውሃ መሰረት የሆኑት የጣና ገባር ወንዞች ከሆኑት ርብና ጉማራ መካከል ይጠቀሳሉ።

ደብረታቦር የአጼ ዮሀንስ 4ኛ ቤተመንግሥት ሰመርንሃም ይገኝባታል። አጼ ዮሀንስ 4ኛ በነገሱበት ወቅት በክረምት ወቅት ቤተመንግስታቸውን ደብረታቦር ሰመርንሀ በማድረግ ያሳልፉ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይገልጻሉ።

ደብረታቦር በቅርብ እርቀት የአጼ ሱሲኒዮስ የታሪክ አሻራ የሚገኝበት የአሪንጎ አቦ ቤተመንግሥት አንዱ ሊጎበኙ ከሚገባቸው ታሪካዊ ቦታዎች መካከል ነው። የቅኔው መገኛ፣ የመሳፍንቶችና የነገስታቶች የብዙ ዘመን መገማሸሪያ፣ ተስማሚ የአየር ጸባይን የተጎናጸፈችው ደብረታቦር እድገቷ ታሪኳን የሚመጥን እንዳልሆነ የተመለከታት ይመሰክራል። ከጣና 50 ኪሜ ብቻ የምትርቀው ደብረታቦር ነዋሪዎቿ የውሃ ጥም እሮሮ በየጊዜው ያሰማሉ። ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መስህቦችን ያቀፈችው ደብረታቦር፣ የጋፋት የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ መንደር መገኛ የሆነችው ከተማ እድገቷ ከታሪኳ ጋር መገጣጠም አቅቶት ተመልክተናል። ለምን እንዲህ ሆነ የሚለውን ጥያቂያችን ይዘን አንዳንድ አካላትን ለማያገር ሞክረን ነበር። አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት በዘመነ ኢህአዴግ መራሹ የወያኔ መንግስት ከተማዋ ከፍተኛ የሆነ ቂም የተያዘባት ጥርስ ውስጥ የገባች ስለነበረች እንደሆነ ይናገራሉ። ወያኔ ከደርግ ጋር በሚያደርገው ፍልሚያ የደብረታቦር እና አካባቢው ህዝብ ለሶስት ተከታታይ አመታት ያለማቋረጥ ሀገራችን በዘር ቅርጫ ለሚከፋፍል፣ አማራን ጠላቴ ብሎ ለመጣ ጨካኝ ሀይል መንገዳችን አንከፍትም ሀገራችንም አሳልፈን አንሰጥም በሚል በርካታ መስዋዕትነት ተከፍሏል። በጉና ተራራ የከፈሉትን ዋጋ ወያኔዎች ደጋግመው በዶክመንታሪና በመጽሀፍ መልክ ያቀርቡት ነበር። በዚህ የተነሳም ወያኔ በትረ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ በአካባቢው እየዞረ በወቅቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበሩ ግለሰቦችን፣ ታዋቂ ሰዎችን አፍኖ በመሰወር፣ በመግደል አካባቢውን ተበቅላለች። ወያኔ አካባቢው በልማት የተዳከመ እንዲሆን አበክራ ሰርታለች። ደብረታቦርን የሚያህል ትልቅ ከተማ የአስፋልት መንገድ የተገነባው 2000 ዓ/ም በኋላ ነበር።

ደብረታቦር የደቡብ ጎንደር ዞን መቀመጫ በመሆን እያገለገለች የምትገኝ ከተማ ናት። ከ1996 ጀምሮ በከተማ አስተዳደርነት ተደራጅታ ቆይታለች። በቅርቡ ከተማዋ ወደ ሪጂዮፖሊታን የከተማ ደረጃነት ካደገች በኋላ ከተማዋ በ3 ክፍለ ከተሞችና በ13 ቀበሌዎች ማለትም በ9 የከተማ ቀበሌዎችና በአራት የገጠር ቀበሌዎችን በማካተት ተዋቅራለች።ክፍለ ከተሞች አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ፣ፊታውራሪ ገብርዬ ክፍለ ከተማ እና እቴጌ ጣይቱ ክፍለ ከተማ በሚል የተዋቀሩ ናቸው።

ደብረታቦር በአሁኑ ወቅት በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ይዛ ኢንቨስተሮችን ትጠብቃለች።በሆቴልና ቱሪዝም፣በሪል ስቴት፣በችፑድ ፋብሪካ፣በብረታብረት ኢንጅነሪንግ፣በእንሳስት እርባታና ተዋጽኦ፣በአትክልትና ፍራፍሪ ዘርፍና ሌሎችንም የኢንቨስትመንት አማራጮችን ይዘው ቢመጡ ይጠቀማሉ።

ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ታህሳስ 04 ቀን 2015 ዓ.ም